ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል::
በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚፈጠር ችግርን በግልፅ ተነጋግሮ፣ መፍታትን ባህሉ ባደረገ ማህበረሰብ ውስጥ የስንፈተ ወሲብ ችግር የትዳር አደጋ የመሆኑ ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፡፡
ሀገራችንን ጨምሮ በአፍሪካና በኤዢያ በትዳር ተጣማሪዎች መካከል በግልፅ የመነጋገር ባህል የዳበረ እንዳልሆነ በስነ ማህበረሰብ ሙያተኞች የተጠኑ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ስንፈተ ወሲብ ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ይከሰታል፡፡ አደጋ የሚሆነው ችግሩ መከሰቱ ሳይሆን፣ ጥንዶች በተፈጠረው ችግር ዙሪያ በግልፅ ተወያይተው መፍትሄ ለማፈላለግ ዝግጁ አለመሆናቸው ነው፡፡
![sexual-dysfunction copy]()
በፍቅረኞችም ሆነ በባለትዳሮች መካከል የሚፈፀም ወሲብ፣ ለሁለቱም የእርካታ (የደስታ) ምንጭ መሆኑ ሲቀር ‹‹ለምን?›› ብለን መጠየቅም ሆነ ርዕሰ ጉዳዩን በጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ አለመነጋገር ብዙዎቻችን አንደፍርም፡፡ ፈቃደኝነቱም የለንም፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ሲመጣ፣ ግንኙነቱ በፍቅረኝነት ደረጃ ላይ ያለ ከሆነ በቃሽኝ (በቃኸኝ) በሚል ይቋረጣል፡፡ ትዳር ከሆነም የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ በሀገራችን የተለመደና በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ የመጣ ክስተት ሆኗል፡፡ የሚገርመው ግን በፍቅረኞች (በትዳር) ደረጃ የተመሰረተው ግንኙነት፣ በአንድ ጀንበር ለማፍረስ ሲወሰን እውነተኛው ምክንያት ከመጋረጃ ጀርባ የተደበቀ ነው፤፤ ፍቺ የጠየቀችው ሴቷ ከሆነች ‹‹ይሰክራል፣ ይደበድበኛል፣ ገንዘብ ይደብቀኛል፣ ከእኔ ሌላ ሴት ወዷል ወዘተ…›› በሚል የውሸት ጭንብል ትሸፍነዋለች፡፡ የትዳር ይፍረስ ጠያቂው ወንዱ ከሆነ ደግሞ ‹‹ትጨቀጭቀኛለች፣ ገንዘብ ታባክናለች፣ ከእኔ ይልቅ የምትሰማው ወላጆቿን ነው ወዘተ…›› በማለት ለግንኙነቱ መሻከር ቁልፍ ምክንያት የሆነውን ችግር ወደ ጎን ሲገፋው ይስተዋላል፡፡ ‹‹ችግሩን የደበቀ መድሃኒት አያገኝም›› እንደሚባለው፣ የስንፈተ ወሲብ ጉዳይን በሀገራችን ባህል ለውይይት የማይቀርብ አጀንዳ በመሆኑ፣ የብዙ ትዳሮችን መፍረስ ከመጋረጃ ጀርባ ያለ አብይ ምክንያት ሆኖ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡
በዘርፉ ጥናት ያካሄዱ ሙያተኞች ስንፈተ ወሲብ መፍትሄ ያለው የስነ ልቦና፣ የአካላዊና የአዕምሯዊ ጤና ችግሮች ውጤት ነው ይላሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅት የስንፈተ ወሲብ ችግር ምንነትን፣ መንስኤን፣ አጋላጭ ምክንያቶችን፣ በሀገራችንና በዓለም ላይ ያሉ አማራጭ መፍትሄዎችን እንደዚሁም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ፣ መታወቅ አለባቸው በምንላቸው ሐሳቦች ዙሪያ፣ ሙያዊ ማብራሪያ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
ጥያቄ፡- ስለስንፈተ ወሲብ ችግር ምንነት፣ የተወሰነ አጠቃላይ ሐሳብ ብናነሳና ውይይታችንን በዚሁ ብንጀምረው ጥሩ ይመስለኛል?
ዶ/ር፡- ስንፈተ ወሲብ የሚለውን ቃል፣ ጠበብ ባለው ዐውዱ ሲታይ፣ የወንድም ሆነ የሴት ብልት አለመነቃቃትንና ለግንኙነት ዝግጁ ካለመሆን ጋር የቀጥታ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ስንፈተ ወሲብ ብልት ለግንኙነት ዝግጁ አለመሆን ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም ሰፋ ያለ ትርጓሜ ያለው ነው፡፡ የስንፈተ ወሲብ ችግር በሁለት መንገድ የሚከሰት ነው፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሯዊ በሆነ የአፈጣጠር ችግር ማለትም በክሮሞዞን፣ የሴትነትና የወንድነት መገለጫ በሆኑት የኦቫሪና የቴስትሮን አፈጣጠር ችግር ምክንያት የሚፈጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ከውልደት በኋላ በዕድገት ሂደት በአካላዊ፣ በአዕምሯዊ፣ በስነ ልቦናዊና በአካባቢያዊ ምክንያቶች የሚፈጠር የስንፈተ ወሲብ ችግር ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚፈጠረው ችግር ለግብረ ስጋ ግንኙነት ፈፅሞ ዝግጁ አለመሆንን፣ ጭራሹኑ ስሜት ማጣትን፣ ፍላጎት አለመኖርን፣ የመጨረሻው እርካታ ላይ አለመድረስን፣ የሌላኘውን ስሜት ሳይጠብቁ ፈጥኖ መርካትን፣ ለግንኙነት ዝግጁ ያለመሆንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ጥያቄ፡- በተፈጥሮም ሆነ ከውልደት በኋላ የሚከሰተው የስንፈተ ወሲብ ችግር፣ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር፡- በወንዶችና በሴቶች ላይ የሚከሰተው የስንፈተ ወሲብ ችግር አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ በተፈጥሮ ሴት ሁና የተፈጠረች ቢሆንም፣ ወንድ የመሆንና ሴትን ለማግባት የመፈለግ በሌላም በኩል በአንድ ሰው ላይ የሴትነትና የወንድነት ብልቶች በአንድ ላይ በመፈጠር ምክንያት የስሜት መሳከር በሁለቱም ፆታዎች፣ በተመሳሳይ መልኩ የሚከሰትበት አጋጣሚ እንዳለ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡
ከውልደት በኋላ ከሚፈጠር የወሲብ ችግሮች አንፃር ሲታይ፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት ጭራሹኑ ስሜትም ሆነ ፍላጎት ማጣት ብዙውን ጊዜ በሁለቱም ፆታዎች ላይ ይከሰታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የወሲብ አካል አለመነቃቃት (ዝግጁ ያለመሆን) ችግር በስፋት በወንዶች ላይ የሚታይ ሲሆን፣ ከሚፈፀመው የወሲብ ግንኙነት እርካታ (ደስታን) ማጣትና የመጨረሻው እርካታ ላይ አለመድረስ ሁለቱም ፆታዎች ይጋሩታል፡፡
ሴቶችም ቀደም ሲል ከነበራቸው ጥሩ ያልሆነ የወሲብ ግንኙነት ምክንያት ወሲብ ለመፈፀም ይፈራሉ ወይም ከነጭራሹ ግንኙነቱን ሊጠሉት ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም በፍቅር ከማይመርጡት ሰው ጋር ትዳር የመሰረቱ ሴቶች ወሲብ የደስታ ምንጭ ሳይሆን እንደ አንድ ስራ ይመለከቱታል፡፡ በመሆኑም ከግንኙነቱ እርካታን አይጠብቁም፡፡ ይህ ሁኔታ በወቅቱ ካልተፈታ ወደ ስር የሰደደ ስነ ልቦናዊ ችግርነት መሸጋገሩ አይቀርም፡፡
ጥያቄ፡- የችግሩ መንስኤ ምንድነው ይላሉ?
ዶ/ር፡- የስንፈተ ወሲብ መከሰቻ ምክንያቶች እነዚህና እነዚያ ብቻ ናቸው የሚባልበት አይደለም፡፡ የችግሩ መንስኤ ከወሲብ መፈፀሚያ አካላት ለውጦች እስከ ስነ ልቦናዊ ቀውሶች ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የስንፈተ ወሲብ ችግር መምጫ ምክንያቶች አንድና አንድ የሚባሉ ሳይሆን ድርብርብ ናቸው የሚባለው፡፡
አንዱና ዋናው ምክንያት፣ አካላዊ የጤና ችግሮች ማለትም በአደጋ ምክንያት ወገብ አካባቢ መሰበርና እሱን ተከትሎ የሚከሰት የነርቭ ስርዓት መቃወስ፣ የኩላሊት፣ የጉበት፣ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የካንሰርና የልብ በሽታዎች በተጨማሪም በወንዶች የዘር ፍሬ ማመንጫና በሴቶች የእንቁላል ማኳቻ አካባቢ የሚፈጠሩ የተለያዩ አካላዊ በሽታዎች፣ የደም ስር ችግሮችና የኮሌስትሮል መጠን መጨመር ለስንፈተ ወሲብ ችግር መከሰት መንስኤ ይሆናሉ፡፡ ሌላው መንስኤ የስነ ልቦና መዛባት (መቃወስ) ነው፡፡ ስነ ልቦናዊ መዛባቱ በውጥረት፣ በጭንቀት፣ በድብርት፣ በጫና ውስጥ በመውደቅ፣ በፍርሃትና ከአይናፋርነት ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከስነ ልቦና ምክንያቶች ቀጥሎ ለስንፈተ ወሲብ ችግር መከሰት፣ ከአዕምሮ ጀምሮ እስከ ታችኛው ቅርንጫፍ የነርቭ ስርዓት ድረስ ያለው አካባቢ በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ፣ የነርቭ ስርዓት ጤና መቃወስ ካለ ለችግሩ መከሰት በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወንድ ብልት ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ዝግጁ መሆን የሚችለው፣ የታችኛው የወንድ ብልት ክፍል በደም ሲሞላ ነው፡፡ ነገር ግን የደም ስሮች በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ ሲወድቁ በቂ የደም መጠን ወደ ወንዱ ብልት አይደርስም፡፡ ካልደረሰ ደግሞ የወንድ ብልት ተነቃቅቶ ለወሲብ ዝግጁ የሚሀንበት ዕድል የለም ማለት ነው፡፡
ቴስቴስትሮን የተባለው ስሜት ቀስቃሽ ሆርመን፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራውን በአግባቡ መስራት ሳይችል ሲቀር፣ በብልት አካባቢ በሚሰራ ቀዶ ህክምና ሳቢያ እዚያ አካባቢ ያሉ ነርቮችና ደም ስሮች ሲጎዱ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ባይስክል መንዳት ለስንፈተ ወሲብ ችግር ያጋልጣል፡፡ በሌላኛው ገፅ ደግሞ ሌሎች ህመሞችን ለመፈወስ ተብለው የሚሰጡ መድሃኒቶች ለአብነት የደም ግፊት፣ ለአዕምሮ ህመም፣ ለጨጓራ፣ ለሽንት መሽናት፣ የኮሌስትሮልን መጠን ዝቅ ለማድረግ የሚወስዱትና ለሌሎች የጤና ችግሮች የምንወስዳቸው መድሃኒቶች፣ ለስንፈተ ወሲብ ችግር መከሰት መንስኤም የመሆን ዕድል አላቸው፡፡ በተለይም ከ25 በመቶ በላይ የሚሆነው የወንዶች የስንፈተ ወሲብ ችግር ምክንያቶች፣ ለሌሎች ህመሞች ተብለው ከሚሰጡ መድሃኒቶች ጋር ይቆራኛል፡፡ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ምክንያት ስነ ልቦናዊ ሲሆን፣ ከ40 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የስንፈተ ወሲብ ችግር ከአካላዊ ጤና ጋር የተያያዘ በቂ ምክንያቶች አሉት፡፡
ከላይ በስንፈተ ወሲብ መከሰት በምክንያትነት ከተዘረዘሩት ውጭ በመጠኑ የበዛ አልኮል መውሰድ፣ ሲጋራ ማጨስና ለመዝናኛ ተብለው የሚወሰዱ ሱስ የማስያዝ አቅም ያላቸው መድሃኒቶች ሁለቱንም ፆታዎች ለስንፈተ ወሲብ ችግር ያጋልጣቸዋል፡፡ ሌላውና ለስንፈተ ወሲብ መፈጠር እንደ አንድ ምክንያት መገለፅ ያለበት፣ ሰውነትን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሽባ የሚያደርገው ፓርኪንሰን የተባለው በሽታ ነው፡፡
ጥያቄ፡- የስንፈተ ወሲብ ችግር በሀገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በምን ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው?
ዶ/ር፡- ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱንና መጠኑን በማስፋት ላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሜሪካ ማቹሲስተስ ሆስፒታል የተደረገው ጥናት እንዳመላከተው፣ ከ40 እስከ 70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰዎች 52 በመቶ፣ በድህነት ውስጥ ያሉ 14 በመቶ፣ ትዳር የፈቱ 14 በመቶና የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎች 13 በመቶ ለችግሩ የመጋለጥ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ በቦስትሰን የተካሄደ ሌላ ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ 30 ሚሊየን የሚሆኑ የስንፈተ ወሲብ ችግር ያለባቸው ወንዶች በአሜሪካ ብቻ ይኖራሉ፡፡ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱና ዕድሜያቸው 70 ዓመት ከሞላቸው ወንዶች ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት የስንፈተ ወሲብ ችግር እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡
የስንፈተ ወሲብ ችግር በሀገራችን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያመለክት ጥናት ማግኘት ባለመቻሉ፣ የችግሩን ስፋት በአግባቡ መገንዘብ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ጤና ተቋማትን መሰረት አድርገው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የስንፈተ ወሲብ ችግር በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ በየዓመቱ ግልፅ ምክንያት ሳይቀመጥላቸው የሚፈርሱ ትዳሮች እየጨመሩ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ በኤዢያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ትዳርን የሚያናጉ ምክንያቶችን ለማወቅ በተጠኑ ጥናቶች ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ምክንያት አንደኛው ወገን ሌላኛውን በወሲብ ግንኙነት ወቅት መርዳት ካለመቻሉ (ካለማስደሰቱ) ጋር የተያያዘ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በሀገራችን በግልፅ የወጣ ምክንያት ሳይኖራቸው የሚፈርሱም ሆነ በግጭት የሚናጡ ትዳሮች ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ ምክንያታቸው የስንፈተ ወሲብ ችግር እንደሆነ ይገመታል፡፡
የስንፈተ ወሲብ ችግር የስነ ልቦና፣ የአዕምሮና የአካላዊ ጤና ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ከግለሰቡ እስከ ቤተሰባዊ ሕይወት ድረስ የሚዘልቅ ማህበራዊ ችግርም ጭምር ነው፡፡ አንደኛው ወገን በስንፈተ ወሲብ ችግር ውስጥ አለ ማለት ሌላኛው ወገንም ተጠቂ ከመሆን የሚያመልጥ አይሆንም፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ደግሞ የትዳር መፍረስንና የልጆችን መበተን ያመጣል፡፡ ልጆቹን የሚረዳቸው ቤተሰብ ከሌላ ለረሃብና ለእርዛት ይጋለጣሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በስንፈተ ወሲብ ችግር ሳቢያ ከፈረሱ ትዳሮች የተገኙ ልጆች የማህበረሰቡ ችግር ወደ መሆን ተሸጋገሩ ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ችግሩ ያለበት ሰው ከሚያሳያቸው ምልክቶች ዋና ዋና የሚባሉትን ቢገልፁልኝ?
ዶ/ር፡- ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የስንፈተ ወሲብ ችግር ሲከሰትባቸው፣ በጋራ ወይም በተናጠል ከሚያሳዩዋቸው ምልክቶች ዋና ዋና ተብለው የሚታወቁት ቀጥሎ የምገልፃቸው ናቸው፡፡
– የወሲብ ፍላጎት ማጣት (ለሁለቱም)
– የወሲብ መፈፀሚያ አካላት ለወሲብ ዝግጁ አለመሆን (በወንዶች)
– ለግንኙነት ዝግጁ የሚያደርግ ፍሳሽ በበቂ መጠን አለመመንጨት፣ የሚደረገውን የወሲብ ግንኙነት ደረቅና ህመም የበዛበት ያደርገዋል (ለሴቶች)
– የመጨረሻው የእርካታ ደረጃ ላይ አለመድረስ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ የስንፈተ ወሲብ ምልክቶች ናቸው ተብሎ ይወሰዳል፡፡
ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች የስንፈተ ወሲብ ችግርን ፈጥኖ እርካታ ላይ ከመድረስ በተጨማሪም ከወንዶች ብልት ማነስና ከሴቶች ብልት መስፋት ጋር ሲያያይዙት ይታያል፣ ይህ አስተሳሰብ ሳይንሳዊ መሰረት አለው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር፡- የተጠቀሱ ጉዳዮች ከስንፈተ ወሲብ ጋር የሚያያዙ አይደሉም፡፡ በእርግጥ ፈጥኖ የዘር ፍሬን የማፍሰስ ችግር ያለባቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ለወሲብ ጉጉ መሆን፣ ዘር ፍሬዬ ፈጥኖ ሊፈስብኝ ነው ብሎ መጨነቅና ተጣማሪዬና በወሲብ ማርካት አልችልም በሚል ስሜት ዝግጁ አለመሆን ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች የስነ ልቦና ሙያተኛ ምክር ከተደረገላቸው በቀላሉ ከችግራቸው የሚላቀቁበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ፈጥኖ የዘር ፍቼን ማፍሰስ ከላይ ከዘረዘርናቸው ምክንያቶች ሌላጋር የሚተሳሰሩበት ሁኔታም እንዳለ መገንዘብ ይገባል፡፡ በሌላም በኩል የወንድ ብልት ማነስም ሆነ የሴት ብልት የመስፋት ጉዳይ፣ ለስንፈተ ወሲብ ችግሮች ጋር የሚያስተሳስረው ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለው በመገንዘብ አጠረብኝ ብሎ መጨነቅን ማስወገድ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሰፋብኝ ብሎ ከመሸማቅም ራስን ነፃ አድርጎ በነፃነት ስሜትን ሰጥቶ፣ ስሜትን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- ችግሩን ለይቶ ለማወቅ ተግባራዊ የሚደረጉ ምርመራዎች የትኞቹ ናቸው?
ዶ/ር፡- ትልቁና የመጀመሪያው ምርመራ ሐኪሙ ከበሽተኛው ጋር ስለ ህመሙ አጠቃላይ ሁኔታ በቂ መረጃ ለማግኘት የሚያደርገው ጥልቅ ውይይት ነው፡፡ በውይይቱ የተገኘውን መሰረት በማድረግ የደም፣ የሽንት፣ የሆርሞንና ተያያዥነት ያላቸው ምርመራዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኤምአርአይ እና በሌሎችም ቴክኖሎጂ አመጣሽ መሳሪያዎች፣ የስንፈተ ወሲብ ችግሩን በትክክል መኖሩን እንዲሁም የችግሩን ስፋትና አይነት በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ እናደርጋለን፡፡
ጥያቄ፡- ለመሆኑ የስንፈተ ወሲብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መፍትሄዎች ካሉ ቢገልፁልኝ?
ዶ/ር፡- የመጀመሪያው አማራጭ መፍትሄ በስነ ልቦና ባለሙያ በተጋገዝ ጭንቀትን፣ ፍርሃትን፣ ውጥረትን፣ ድብርትን፣ ስጋትንና ቀድሞ ተሸናፊ የመሆን ስነ ልቦናዊ ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሰጡ ሳይኮሎጂካል ቴራፒዎች አሉ፡፡ ስለሆነም የስነ ልቦና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብሎ በመተግበር፣ ህክምናውን በአግባቡ መፈፀም ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህ ሂደት ደስተኛ የመሆንና በራስ የመተማመን መንፈስም በዚያው መጠን ይዳብራል፡፡ ነፃነት ያለው፣ ከስጋትና ከጭንቀት የፀዳ ግንኙነት በመፈፀም የመጨረሻው እርካታ ላይ የሚደርስበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ጠብቆ ለመዝለቅም የሁለቱን ጥንዶች በአግባቡ ለመደጋገፍ የሚያስችል የቅንነት ባህልን እንዲገነቡ ያስፈልጋል፡፡ ከስነ ልቦናዊ መፍትሄዎች ባሻገር ለስንፈተ ወሲብ ችግር መከሰት ምክንያት ናቸው ብለን ያነሳናቸውን በሽታዎች፣ ለምሳሌ ስኳርንና ደም ግፊትን በአግባቡ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲሁም ሌሎችን የውስጥ ጤና ችግሮችን ጊዜ ሳይወስዱ መታከም ተገቢ ይሆናል፡፡ ለሌሎች በሽታዎች ተብለው የሚሰጡ መድሃኒቶችን በተቻለ አቅም ማስወገድ ይገባል፡፡ በሌላም በኩል የስንፈተ ወሲብ ችግርን በጊዜያዊነት ቢሆን መፍትሄ ለመስጠት የሚችሉ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሲልደናፊል (በንግድ ስያሜው ቪያግራም)፣ ቮርድናፍና ታላፌን የሚባሉት በዓለም ላይ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሲልደናፊል (በንግድ ስያሜው ቪያግራም) የሚባለው መድሃኒት በሀገራችንም ይገኛል፡፡ ይህ መድሃኒት በዋጋው ተመጣጣን የሚባል ነው፡፡ እዚህ ላይ ማንኛውም ሰው መገንዘብ ያለበት፣ መድሃኒቱ መወሰድ ያለበት ሌሎች ስነ ልቦናዊ ችግሮችን ለማስወገድና መፍትሄ ማምጣት ሳይቻል ሲቀር ብቻ ይሆናል፡፡
ሌላው አማራጭ ህክምና፣ በሆርሞን እጥረት የተነሳ የስንፈተ ወሲብ ችግር ለአጋጠማቸው ሰዎች፣ የሆርሞን መተኪያ ህክምና ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ የህክምና ዘዴ በሀገራችንም የሚሰጥ ነው፡፡ ከላይ በገለጽናቸው አማራጭ ህክናዎች መፍትሄ ላላገኙ ሰዎች፣ ምንም እንኳን የህክምና ዘዴዎች በሀገራችን ባይገቡና ጥቅም ላይ ባይውሉም በሌላው ዓለም የሚሰራባቸው ሌሎች ተጨማሪ መፍትሄዎች አሉ፡፡
– ቫኪዩም ዲቫይስ የሚባል ዘዴ አለ፤ ይህ ዘዴ የወንድ ብልት እንዲቆም በማድረግና ቫኪዩም ዲቨይሱን ብልት ላይ በመግጠም ወዲያውኑ ውጤታማ ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ያስችላል፡፡
– ብልት በበቂ መጠን ወሲብ መፈፀም እንዲችል የተነቃቃና ለወሲብ የተዘጋጀ፣ የወንድ ብልት ላይ የሚወጉ መድሃኒቶች በዓለም ገበያ ላይ አሉ፡፡
– ውጤታቸው አስተማማኝነቱ የሚያጠራጥር በመሆኑ፣ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ጠንካራ ስለሆና አንዳንድ ጊዜ ተመልሶ የማይተኛ የብልት መቆምን የሚያመጡ በመሆናቸው፣ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር ጥቅም ላይ አይውሉም እንጂ በሽንት ቧንቧ ወደ ውስጥ የሚጨመሩ የስንፈተ ወሲብ ችግር መድሃኒቶች በሌሎች የዓለም ሀገሮች በስፋት ይሸጣሉ፡፡
– በቀዶ ህክምና ብልትን በመሰንጠቅ፣ ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ማቆሚያ በማስገባት፣ ውጤታማ ወሲብ መፈፀም የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡
– የስንፈተ ወሲብ ችግሩ ዋነኛ መንስኤ በደም ስር ላይ የተከሰተ የጎላ ጉዳት መሆኑ በምርመራ ከተረጋገጠ፣ ደም ስሮቹን በማይክሮ ሰርጀሪ የማስተካከልና ጤናማ የሚያደርግ የህክምና ዘዴም በሌላው ዓለም ወደ ተግባር ከተሸጋገረ ከርሟል፡፡
ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ቪያግራምንም ሆነ ሌሎች መድሃኒቶችን በራሳቸው ሲወስዱ ይስተዋላል፣ እንዲህ ያለው ተግባር ችግር አያስከትልም?
ዶ/ር፡- ቪያግራም ማንኛውም ሰው የሚወሰደው መድሃኒት አይደለም፡፡ መድሃኒቱ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የልብና የኩላሊት በሽታዎችን ያባብሳል፡፡ እንደዚሁም የደም ስሮችን በማጥበብ ስትሮክንና ደም ማነስን ያመጣለ፡፡ እነዚህ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች በምንም ምክንያት ቪያግራን መውሰድ የለባቸውም፡፡ ስለሆነም በምንም መንገድ ቢሆን ቪያግራም ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መወሰድ የለበትም፡፡ መድሃኒቱ በሐኪም ትዕዛዝ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ከተወሰደ ሱስ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ሱስ ከሆነ መድሃኒቱ ካልተወሰደ በስተቀር ወሲባዊ ግንኙነት መፈፀም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡ ሌሎችም መድሃኒቶች ተመሳሳይ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ስላላቸው በተቻለ አቅም አግባብ ያለው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ጥያቄ፡- ለማጠቃለያ ማንሳት የሚፈልጉት ሐሳብ ካለ ያንሱትና እንሰነባበት?
ዶ/ር፡- የስንፈተ ወሲብ ችግር ሊታከምና ሊድን የሚችል የጤና ችግር መሆኑን ሁሉም ሰው ቢገነዘብ ጠቃሚ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለቱ ተጣማሪች የተሰማቸውን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ከደመባበቅና ወደ ተባባሰ የስነ ልቦና ችግር ከማምራት ይልቅ በግልፅ መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ መፍትሄ ባለው ችግር ግንኙነታቸውን ጤናማ ወዳልሆነ አቅጣጫ መምራት አይኖርባቸውም፡፡ ስለሆነም በተፈጠረው ችግር ዙሪያ መደማመጥና መከባበር በሰፈነበት አግባብ፣ የመነጋገር ልምድን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የስንፈተ ወሲብ ችግር ከተከሰተ በኋላ ማከም ብቻ ሳይሆን ችግሩን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችም እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ለአብነት ጭንቀትን፣ ድብርት፣ መረበሽንና ፍርሃትን መቀነስ ከተቻለም ጭራሹኑ ማስወገድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም አልኮልን አዘውሮ ከመውሰድ መታቀብ፣ ጫት መቃምና ሲጋራ ማጨስን በተቻለ መጠን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በተፈጥሮ የተከሰተ የስንፈተ ወሲብ ችግር መኖን አለመኖሩን ለማረጋገጥ፣ ልጆች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ቢመረመሩና ችግሩ ካለ ቢታከሙ ጠቃሚ ይሆናል፡፡